girls in masks outside school

የተወደዳችሁ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ ሰራተኞች እና ተማሪዎች፦

የትምህርት ቦርድ ኤፕሪል 20 ባደረገው የቢዝነስ ስብሰባ ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለመክፈት፣ MCPS እያከናወነ ባለው የማገገሚያ ጥረት ላይ ተወያይቷል። እስካሁን ድረስ ከ60,000 በላይ የሚሆኑ ከመዋእለ ህጻናት እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በአካል ወደ ትምህርታቸው ተመልሰዋል። ሠራተኞቻችን እና ተማሪዎቻችን በዚህ የሽግግር ወቅት ከአዳዲስ አሠራሮችና የጤና አጠባበቅ ጥንቃቄ በመጠበቅ ከፍተኛ ሥራ አከናውነዋል። ተማሪዎች ከእኩዮቻቸው ጋር ለመገናኘት፣ በስፖርትና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የሚችሉባቸው እድሎችን ወደሚያገኙበት ሕንፃዎች በመመለሳቸው ደስተኞች እንደሆኑ ከማህበረሰቡ ሰምተናል። ብዙዎቹ የ MCPS ቤተሰቦች ቨርቹወል ትምህርት ላይ ለመቆየት መርጠዋል፤ እነርሱም ተማሪዎችን የሚያሳትፍ ትምህርት በማግኘት ይቀጥላሉ። ይህ በትምህርት ቤት የተለመደ ተሞክሮ እንዳልሆነ ስለምናውቅ ማህበረሰባችን ሁኔታውን በጥንካሬ ለመቋቋም በመቻሉ አመስጋኞች ነን።

ከቦርድ ስብሰባ ማወቅ የሚያስፈልጋችሁ ስድስት ነገሮች እና ወደፊት ቀጣዩ ምን እንደሚሆን ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፥

  1. ትምህርት ቤቶች የተጠባባቂዎችን ዝርዝር ለማጥራት እየሰሩ ሲሆን ለቀሪው የትምህርት ዓመት በ A/B ፈረቃ ይቀጥላሉ። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ከተጠባባቂ ዝርዝር በአካል መጥተው እንዲማሩ ከቤተሰቦች ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ናቸው። እነዚህ ዝርዝሮች፣ ዲሰምበር 2020 ይፋዊ የዳሰሳ ጥናቱ ከተዘጋ በኋላ ክፍል ውስጥ በአካል የሚሰጠውን ትምህርት የመረጡ ተማሪዎችን ይመለከታል። በመጠባበቂያ ዝርዝር ላይ ማሻሻል/ለውጥ ለማድረግ ብንችልም በየሳምንቱ የሚደረገውን ፈረቃ ማስወገድ የተማሪዎችን ተሞክሮና ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን የክፍል አስተማሪ ምደባ እና የጊዜ ሠሌዳ በእጅጉ ይነካዋል። በተጨማሪም በየደረጃው ተጨማሪ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ አኳያ መመሪያውን በመጠበቅ የተማሪዎችንና የሠራተኞችን ጤንነት እና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ በቂ ቦታ መኖርም እጅጉን ወሳኝ ነው። ትምህርት ቤቶች በተቻለ መጠን ብዙ ተማሪዎችን በአካል ማስተናገድ እንዲችሉ በሕንፃዎቻቸው ውስጥ አመቺ መርኃግብሮችን የመተግበር/የመጠቀም መመሪያዎችን ያካትታሉ። የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) የመማሪያ ክፍልን የአካላዊ ርቀት መመሪያ ከ 6 ጫማ ወደ 3 ጫማ ያሻሻለ ቢሆንም አሁንም 6 ጫማ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊ ለሆነባቸው በርካታ አካባቢዎች ይኼ የሚመከር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት እሮብ ቀን ለሁሉም ተማሪዎች ቨርቹወል የትምህርት ቀን መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፥ የሚቻልበትን ሁኔታ በመፈለግ ረቡዕ ዕለትን ተማሪዎች በአካል ወደ ት/ቤት መጥተው የሚማሩበት ቀን እንዲሆን ቦርዱ ለ MCPS ጥያቄ አቅርቧል።
  2. MCPS ፎል ላይ ተማሪዎች በሙሉ በሣምንት አምስት ቀን በአካል ተገኝተው የሚማሩበት መርሃግብር እያቀደ/እያዘጋጀ ነው። የ 2021-2022 የትምህርት ዓመት ለተማሪዎቻችን እና ለሠራተኞች ይበልጡኑ መደበኛ/የተለመደው አይነት የትምህርት ዓመት እንደሚሆን ይጠበቃል። በሕዝብ ጤና ላይ በየጊዜው መሻሻሎች መታየታቸው፣ ክትባቶች መበራከታቸው እና እገዳዎችን ማላላታቸው ብዙ ተማሪዎች በአካል ት/ቤት ተገኝተው እንዲማሩ እና መደበኛው የትምህርት አሠጣጥ እንደገና እንዲቀጥል ማስቻሉ አይቀርም። ሰራተኞችን፣ ተማሪዎችን፣ እና ቤተሰቦችን እንደገና ወደ ትምህርት ቤት ህንፃዎች ሲመለሱ የጤና አጠባበቅ መመሪያዎችን እና ፕሮቶኮሎችን ለመጠበቅ ከአካባቢ፣ ከስቴት እና ከአገር አቀፍ የጤና ባለሙያዎች/ሃላፊዎች ጋር በቅርበት መስራታችንን እንቀጥላለን። ፎል ላይ በተሳካ ሁኔታ ዳግም ለመክፈት እቅድ ማውጣታችንን የምንቀጥል ሲሆን፥ ሠመር ላይ ለህብረተሰቡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችን እናደርሳለን።
  3. ትምህርት ቤት በሚሰጠው ኮቪድ-19 ምርመራ ላይ መሳተፍ የሁላችንንም ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳል። በዲስትሪክቱ በየጊዜው በርካታ ሰዎች ላይ የሚደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ በቀጣይነት ይከናወናል። በአሁኑ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለምርመራ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ትምህርት ቤቶችን እና የእርስ በርስ ጤንነትና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለመርዳት፣ እባክዎ የስምምነት ቅጽ ሞልተው በተቻለ ፍጥነት ይመልሱ። ስለ ኤፕሪል ምርመራ መርሀ ግብር እዚህ መመልከት ይችላሉ። የሜይ ወር ካለንዳር በዚህ ሣምንት ኤፕሪል 26 በሚጀምረው ሳምንት ድረገጽ ላይ ይለጠፋል። ለማስታወስ ያህል፥ በአካል ከሚማሩ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ውስጥ ኮቪድ-ፖዘቲቭ ከሆኑ ክትትል እየተደረገ ሪፖርት ይደረጋል። በሽታው ሊተላለፍ በሚችልበት ጊዜ ላይ በቦታው ተገኝተው ከሆነ (ምልክት ከመታየቱ ወይም ምርመራ ሳይደረግላቸው ሁለት ቀን በፊት ተብሎ እንደተገለጸው) ሠራተኞችን እና/ወይም ተማሪዎችን የሚመለከት ኮቪድ-19 ፖዚቲቭ ኬዝ ከተገኘ በጠቅላላ ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ ይገለጻል። ሠራተኞችን ወይም ተማሪዎችን የሚመለከቱ በቦታው ባልተገኙ ጊዜ የተደረገ (ስፕሪንግ የእረፍት ወቅት ወይም ቨርቹወል ብቻ የሚከታተሉና በስፍራው ያልተገኙ) የምርመራ ፖዚቲቭ ኬዞች ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ አይገለጹም። በተጨማሪም አንድ ተማሪ ወይም የሥራ ባልደረባ በምርመራ ፖዚቲቭ ባይሆኑም በመጋለጣቸው ምክንያት ራሳቸውን አግልለው በሚቆዩበት ወቅት የማህበረሰብ ደብዳቤ አንልክም። በሚቀጥለው ወር MCPS የሠራተኞችንና የተማሪዎችን የኮቪድ ኬዝ መረጃ የሚያካትት አዲስ ዳሽቦርድና የመረጃ ቋት ይዘረጋል። በ MCPS ድረገጽ ላይ ይገኛል።
  4. በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ለአንደኛ፣ ለመካከለኛ፣ እና ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተፋጠኑ ኮርሶችን መስጠት እንደተጠበቀ ነው። ብሔራዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ከመዋእለ ህጻናት እስከ 12ኛ ክፍል (K-12) ከማናቸውም ሌሎች ትምህርቶች ይልቅ በሂሣብ ትምህርት ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። MCPS ይህን የባከነ ትምህርት ለማሻሻል/ለመቅረፍ የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፏል። በ ሜይ 25  የትምህርት ቦርድ ስብሰባ ላይ ስለ MCPS የሒሳብ ትምህርት ዕቅድ ተጨማሪ መረጃ ይቀርባል።
  5. MCPS ቨርቹወል አካዳሚ ፎል ላይ የሚጀምር ሲሆን ከቅድመ መዋእለ ህጻናት እስክ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ዓመቱን በሙሉ ቨርቹወል አማራጭ ይሰጣል። በወረርሽኙ ወቅት ቨርቹወል ትምህርት ለብዙ ተማሪዎች አስቸጋሪ ቢሆንም ሌሎች ግን አዳብረውታ። በኢንተርኔት ማስተማርና መስራት እንደአመቺነቱ (Flexible) መደረጉ በርካታ የቤተሰብ ፍላጎቶችንና የአንዳንድ ተማሪዎችን የማኅበራዊ ስሜት ፍላጎት የሚደግፍ እድል አስገኝቷል። በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች፣ MCPS ኦንላይን የመማር ማስተማር አማራጮችን ለመገንባት እና ለማሻሻል አቅዷል። በመጪዎቹ ቀናት ወላጆችና ተማሪዎች ስለ ቨርቹወል አካዳሚ ዝንባሌ/ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት የመሙላት እድል ይኖራቸዋል። ይህ ስለ ቨርቹወል አካዳሚ የቤተሰብን ፍላጎት ለማወቅ ብቻ ነው እንጂ መቀበያ/ምዝገባ አይደለም። ለቨርቹወል አካዳሚ እንዴት ማመልከት እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ በቅርቡ ለማህበረሰቡ ይገለጻል።
  6. ሁሉም የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከህንጻ ውጪ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ያከናውናሉ። እገዳው ተሻሽሎ ለአንድ ተመራቂ ሁለት እንግዶች እንዲፈቀድ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፐብሊክ ስኩልስ (MCPS) ከሞንትጎመሪ የጤናና ሰብዓዊ አገልግሎቶች ዲፓርትመንት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል። ትምህርት ቤቶች በመጪዎቹ ሳምንታት ስለሚያከናውኑት ሥነ ሥርዓት ለቤተሰቦች ዝርዝር መረጃ ይሰጣሉ። በተጨማሪም፥ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ የቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ወቅታዊ እገዳዎች ስላሉ እና በአንደኛ ደረጃ እና በመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሚድልስኩል) ከቤት ውጪ የሚደረጉ ሁነቶችን ከማስተናገድ ጋር ተያይዞ ባለው ውስንነቶች ምክንያት MCPS ለ5ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ የሚዛወሩበት ስነ-ስርአት ቨርቹወል እንዲከናወን ምክረሃሳብ ይሰጣል። ትምህርት ቤቶች የ5ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን በአካል ተገኝተው ወደ ሚቀጥለው የክፍል ደረጃ የሚዛወሩበትን ክንውን ለማክበር የሚያስችሉ ተጨማሪ መንገዶችን እየፈለጉ ናቸው።

በዚህ የትምህርት ዓመት ሰባት ሳምንታት የቀሩ ሲሆን በጠንካራ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ቁርጠኞች ነን። በቀጣይነት ስለሚደረግልን ድጋፍ እናመሰግናለን።


መገልገያዎች/ሪሶርሶች



Email us: ASKMCPS@mcpsmd.org

Montgomery County Public Schools