Virtual Civility
Guidance for Students and Families

ቨርቹወል ትህትና
ለተማሪዎች እና ለቤተሰቦች መመሪያ

ወላጆችና ሞግዚቶች በተማሪ ውጤታማነት ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን ድጋፋቸውም በተለይ ቨርቹወል በመማር ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው።

አስተማሪዎች ከርቀት ሲሠሩና ልጆች ቤት ውስጥ እየተማሩ አልፎ አልፎ የመቋረጥ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ይሁን እንጂ ኦንላይን የመማሪያ ክፍል እንደ እውነተኛ የመማሪያ ክፍል በመሆኑ፥ በዚሁ አይነት መታየቱ አስፈላጊ ነው።

ቨርቹወል መማር ለማንኛውም ሰው አዲስ ነው። ቨርቹወል ትምህርት ለማግኘት እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ማድረግና ትዕግሥት በጣም አስፈላጊ ነው። ትምህርት ቤቶቻችን ተማሪዎችን ለመደገፍ እያከናወኑት ያለውን ሥራ እንዲሁም ወላጆችና ሞግዚቶች ለተማሪ ስኬት የሚጫወቱትን ሚና እናከብራለን-እናደንቃለን።


ለወላጆች መመሪያ

 
 • ኦንላይን ትምህርት ልክ እንደመደበኛው "የትምህርት ክፍል" መታየት ስላለበት ይህንኑ ስርዓት መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የእርስዎ ልጆች በትምህርት ገበታቸው ላይ ሠዓት አክብረው መገኘታቸውን፣ ለመማር ዝግጁ መሆናቸውን፣ ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት መሳተፋቸውን፣ የትምህርት ክፍል ደንብ እንደሚያከብሩና እንዲሁም የ MCPS የተማሪ ስነምግባር ደንብ የሚጠብቁ መሆናቸውን ያረጋግጡ። በቨርቹወል ትምህርት ወቅት "በእውነተኛ ሕይወት" የሚያደርጓቸውን ተመሳሳይ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል ያስፈልጋል።
 • የቨርቹወል ትምህርት አለም ለሁላችንም አዲስ ነው። አንዳንድ ጊዜ የመቆራረጥ ወይም የቴክኒክ ችግር አልፎ አልፎ ሊያጋጥም እንደሚችል እንረዳለን። "እንደ ትምህርት ቤት" የሚያገለግል ሥፍራ መርጠው ያዘጋጁ፣ እንዲሁም ቴሌቪዥን፣ ሞባይል ስልክና ሙዚቃ የመሳሰሉ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ለማስወገድ-ለመቀነስ የተቻለዎትን ሁሉ ያድርጉ።
 • ትምህርት ቤት ማለት ተማሪዎች ግንዛቤአቸውን-መረዳታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት የጥሞና ሥፍራ መሆኑን ያስታውሱ። ይህም አስተማሪዎች ጠንካራ ጎኖችንና ድክመቶችን ለይተው እንዲያውቁና የትምህርቱን አቀራረብና የማስተማር ዘዴ እንዲለዩ ይረዳቸዋል።
 • የሐሳብ ልውውጥ/ኮሙኒኬሽን፦ ስለ እርስዎ ልጅ የእድገት ደረጃ ከአስተማሪው(ዋ) ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ።
 • አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጆችዎን በሥራቸው ይርዷቸው፤ ሆኖም እነርሱ መሥራት ያለባቸውን ሥራ እርስዎ አይጨርሱ ወይም መልሱን አይስጡ።
 • የልጅዎ ካሜራና ማይክሮፎን ምን ሊያነሳ እንደሚችል እንዳትዘነጉ።
 • ልጅዎ ትምህርት ቤት ለመሄድ በትክክል መልበስ እንዳለበ(ባ)ት፣ እንዲሁም ቤት ውስጥ የሌሎችንም አለባበስ በአግባብ መሆኑን በማረጋገጥ ይርዱ።
 • የሌሎች ተማሪዎችና ቤተሰቦችን ግላዊ ገመና ማክበር አስፈላጊ ነው። የልጅዎን ክፍል ፎቶዎች ወይም ቪዲዮዎች በማኀበራዊ ድረ ገጾች መለጠፍ እንደማያስፈልግ ሁሉ ፈቃድ ሳይሰጥ የማስተማር ክፍለጊዜዎችን መቅዳት ክልክል ነው።
 • የትምህርት ሠዓት ይከበር፦ ለተማሪዎችዎ የትምህርት ሠዓት መሆኑን በመደበኛ የጊዜ ሠሌዳ ላይ ያስቀምጡ፣ ይህ ክፍለጊዜ ወላጆች ስለተማሪው(ዋ) ጉዳዮች የሚነጋገሩበት/የሚወያዩበት ሠዓት ወይም ትምህርት የሚያቋርጡበት ጊዜ አይደለም።

ለአስተማሪዎች እና ለትምህርት ቤት ሠራተኞች ኢ-ሜይል በሚልኩበት ጊዜ፦

 • ስለ ጉዳዩ ገላጭ መስመር ይጠቀሙ።
 • ውጤት ለማግኘት ስለሚፈልጉት ጉዳይ ግልጽ ያድርጉ።
 • የልጅዎን ሙሉ ስም፣ የእርስዎን ስም እና የግንኙነት መረጃ ይግለጹ።
 • አስተማሪዎች ሥራ ስለሚበዛባቸው፥ ከወላጆች ለሚላክላቸው ኢ-ሜይሎች መልስ ለማግኘት በቂ ጊዜ መስጠት አለብዎት።

ለተማሪዎች መመሪያ

 • ለመማር እና በትምህርት ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅታችሁ መግባት አለባችሁ፥ የትምህርት ክፍል ህጎችን መከተል እና የ MCPS የተማሪ ስነምግባር ደንብ ማክበርና መከተል ይኖርባችኋል።
 • ኦንላይን ትምህርት ልክ እንደመደበኛው የትምህርት ክፍል መሆኑን መገንዘብ እና አስተማሪዎች በሚያስተምሩበት ሠዓት በማቋረጥ ጣልቃ መግባት እና አስተያየት ለመስጠት መሞከር ተገቢ አለመሆኑን መዘንጋት የለበትም።
 • አስተማሪ በቀጥታ ትምህርት በሚሰጥበት-በምትሰጥበት ወቅት ማቋረጥ፣ ከአስተማሪ ጋር መነጋገር ወይም ጣልቃ መግባት አያስፈልግም። አስታውስ(ሺ)፥ ከአስተማሪ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዝ ያስፈልጋል።
 • በኢ-ሜይል ወይም በማንኛውም ሌላ ኮሙኒኬሽን አስተማሪዎችን በትህትና አክብር(ሪ)፣
 • ከቤት ውስጥ ማንኛውም ወደካሜራ የሚቀርብ ሰው በተገቢ ሁኔታ መልበስ አለበ(ባ)ት።
 • ያለፈቃድ የትምህርት ክፍለጊዜዎችን ሪኮርድ ማድረግ ክልክል ነው። በክፍል ውስጥ ለሚከናወነው ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ወሳኝ መረጃዎችን ለመያዝ ካልሆነ በስተቀር
 • ትምህርት በሚተላለፍበት ወቅት ጣልቃ አትግባ(ቢ)። ከአስተማሪህ(ሽ) ጋር መነጋገር ካስፈለገ፣ ለኮንፈረንስ ጊዜ እንዲመደብ ኢሜይል ጻፍለ(ላ)ት።
 • ካሜራው ወይም ማይክሮፎኑ ምን ሊያነሣ እንደሚችል አትዘንጋ(ጊ)።
 • ቨርቹወል መማር ለማንኛውም ሰው አዲስ ነው። ትምህርት ቤቶቻችን እናንተን ለመደገፍ እያከናወኑት ያለውን ሥራ እንዲሁም ወላጆች/ሞግዚቶች ለእናንተ ስኬት የሚጫወቱትን ሚና እናከብራለን-እናደንቃለን።